“ለማ መገርሳን የቀነሰ መደመር፣ መደመር አይሆንም” ዶ/ር ሔኖክ ገቢሳ

ሬዲዮው አክሎም አቶ ታዬ፣ “አቶ ለማ በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ውህደቱ አስፈላጊ እንደሆነና የመደመር ዕሳቤ ከኢትዮጵያ ዐልፎ ለምሥራቅ አፍሪካም ጠቃሚ ሃሳብ እንደሆነ ተስማምተው ነው ያጸደቁት፤ የልዩነት ሃሳብ አልሰማንም። ከዚያም አልፎ በኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴና ጉባኤ፣ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ሁሉ የተለየ አቋም አላንጸባረቁም። በዚህ መሄድ አለብን የሚል የተለየ አማራጭ ሃሳብም አላቀረቡም” ማለታቸውን አስታውቋል።

ይህንን የአቶ ለማ አቋም አስመልክተን ያነጋገርናቸው በዋሺንግተንና ሊ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሔኖክ ገቢሳ (ዶ/ር) ውህደት ብለን የምንናገር ከሆነ ለዚች አገር ከፍተኛ ውለታ ዋሉ እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉትን ሰዎች እየቀነስን ውህደቱን እውን ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለውናል።

ዶ/ር ሔኖክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን፣ ሀሳባቸውንና እምነታቸውን ሳያካትቱ ውህደቱን ማካሄድ ከባድ ይሆናል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ፣ ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ‘ለዐቢይ ትልቁ ተግዳሮት የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መርቶ ማሻገር ሳይሆን ኢህአዴግን እንደ ኢህአዴግ መርቶ መሻገር መቻልና አለመቻል ላይ ይመሰረታል’ ማለታቸውን በማስታወስ፣ በአሁኑ ሰዓትም በግንባሩ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች መጠላለፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖበታል ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።

“ከዚህም የተነሳ እንደሚፈለገው አብሮ ወደፊት መሄድ አልቻሉም” በማለት የእርሳቸው ፓርቲ ኢህአዴግ ተዋሀደም አልተዋሀደም የሚጠብቅበት ነገር እንዳለ አጽንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።

በውህደቱ ላይ አቶ ለማ እንደማይስማሙ በተባራሪ ወሬ ሲሰሙ መቆየታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ሔኖክ ደግሞ፤ እንዲህ ዓይነት መከፋፈል በአሁኑ ሰዓት መፈጠር አልነበረበትም ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።

ለዚህም ምክንያት ነው ያሉትን ሲጠቅሱም፤ “በእነርሱ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት የኦሮሞ ትግል መከፋፈል የለበትም ብዬ ስለማምን ነው” ብለዋል።

“አቶ ለማም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ትልቅ ውለታ የዋሉ ሰዎች ስለሆኑ ሃሳባቸውን ወደ አንድ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል” በማለትም፤ “የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ እንመልሳለን ብለው ካመኑ፤ የኦሮሞ ሕዝብ መሪዎች ነን ብለው ካሉ፤ መደማመጥ አስፈላጊ ነው” ሲሉ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።

የኢትዮጵያ መሪዎች ዲሞክራሲን አንገነባለን ሲሉ ተቃራኒ ሀሳቦችንም ማስታገድ አለባቸው ብዬ አምናለሁ የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ አሁንም ያለመግባባት መንስዔ የሆነው የውህደት ውሳኔ እንደገና መታየት አለበት ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *