የሴይንት ፒተርስበርግ ፖሊስ ቦርሳቸው ውስጥ የተቆረጥ የሰው ልጅ እጅ አግኝቼባቸዋለሁ ያላቸውን የታሪክ ምሁር በቁጥጥር ሥር አዋለ።

ፕሮፌሰሩም ፍቅረኛቸውን እንደገደሉ አምነዋል። ጉምቱው ፕሮፌሰር ኦሌግ ሶኮሎቭ ሰክረው ወንዝ ውስጥ ወድቀው ነው የተገኙት። ወንዝ አካባቢ የተገኙትም እጁን ሊጥሉት ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

ሰውዬው ከተያዙ በኋላ ቤታቸውን የፈተሸው ፖሊስ የፕሮፌሰሩ የቀድሞ ተማሪ የነበረች የ24 ዓመት ወጣት ሬሳ አግኝቷል። የፕሮፌሰሩ ቤት ውስጥ ጭንቅላቷ ተቆርጦ ሬሳዋ የተገኘችው ሴት አናስታሲያ የሺቼንኮ ከፕሮፌሰሩ ጋር በርካታ ፅሑፎች ያሳተመች ተማሪ ናት።

የናፖሌዮን ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሶኮሎቭ በፈረንሳይ የሌጌዎን ክብር የተሰጣቸው ሰው ናቸው። የግለሰቡ ጠበቃ የሆኑ ሰው ፕፎፌሰሩ ፍቅረኛቸው የነበረችውን ወጣት መግደላቸውን አምነዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የ63 ዓመቱ ፕሮፌሰር የወጣቷን ሬሳ ካስወገዱ በኋላ እንደናፖሌዮን ለብሰው አደባባይ ላይ ራሳቸውን ሊያጠፉ አስበው እንደነበርም ታውቋል። ግለሰቡ ከፍቅረኛቸው ጋር ባለመግባባታቸው ምክንያት እንደገደሏትና ጭንቅላቷን እንደቆረጡ ለፖሊስ አምነዋል።

የፕሮፌሰሩ ጠበቃ የሆኑት ሰው ደንበኛቸው ‘ሂፖተርሚያ’ [ሰውነት ከፍተኛ የሙቀት መጠን ሲያጥረው የሚከሰት በሽታ] የተሰኘ በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን አውስተው የጭንቀት ተጠቂ ሳይሆኑ አይቀርም ብለዋል።

የታሪክ ተመራማሪው ስለ ናፖሌዮን በርካታ መፃሕፍትን ፅፈዋል። አልፎም በርካታ ፊልሞች ላይ የታሪክ ተመራማሪ እና አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።

የፈረንሳይ ማሕበራዊ ፍትህ፣ ኢኮኖሚክስ እና ፖለቲካ ኢንስቲትዩት አባልም ነበሩ። ነገር ግን ዜናውን የሰማው ይህ የተከበረ የት/ት ተቋም ግለሰቡን ከአባልነት ሰርዟል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *